ምኒልክ በአዳም ልጆች መለኪያ የማይለካ መለከታዊ ባህሪ ያለው ያህል ገዝፎ እንዲታይ ያደረገው ምኒልክ የደጃፉን ጎተራ አራግፎም ሆነ የበረቱን ከብት ጎትቶ አውጥቶ ሽጦ በገዛው ስናድር ፣ለቨን ( ነፍጥ ) ሳይሆን ምኒልክ የጠቀመበትን መሳሪያ የተገዛው
ሥጋን በኩበት ጠበሱት
ምኒልክ የአያቱን የሸዋው ንጉስ ሳህለ ሥላሴን ህልም ዕውን ለማድረግ የተፈጠረ መሆኑን ከተነገረው ጊዜ ጀምሮ የአያቴን ርስት እስኪመለስ ሲል ታትሯል ፡፡ምኒልክ ከ1860ዎቹ ጀምሮ የሸዋን የስልጣን ወሰን ለማስፋት በአጎራባቾቹ ላይ ዘመቻ አካሒዶ በ1869 አስከ 1876 ዓ/ም ባለው ጊዜ ዉስጥ የሸዋን ግዛት በእጄ ለማለት ቻለ ፡፡ ነገር ግን በ1882 ዓ/ም የትግሬው ደጃች ካህሳይ ምርጫ ወይም ዮሓንስ 4ኛ የተባለው ምኒልክ ሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ሳንካ እየፈጠረ አስቸገረው ፡፡ ምኒልክ በሰሜን በተነሳው ካህሳይ ምርጫ ወይም አፄ ዮሓንስ 4ኛ ምክንያት ወደ ሰሜን ከመንሰራፋት ይልቅ ወደ ደቡብ ፣ ደቡብ ምዕራብ ፣ምዕራብ እና ወደ ምስራቅ ወረራዉን በስፋት ገፋበት ፡፡
እንዲህም እየተባለለት ፣-
የሚጓዘው ሰንጋ የሚነዳው ሻሂር ለልደት ባይደርስ ፣
እሱስላም( እስላም ) አርዶ ዋለ የሸዋው ንጉስ ።
ከወደ ሐረር እና አርሲ ሲዘምት ፀሐይቱ ነች የገጠመችው ።
እነዚህ አዳዲሶቹ አከባቢዎች ላይ የትግሬና የጎጃሙን አከባቢ ያህል የተደራጀ ኃይል እምብዛም ባለመኖሩ የተነሳ ዘመቻዎቹ ያለብዙ ሳንካ የመስፋፋቱ በዘላቂነቱና ትርፋማነቱ ለምኒልክ የሞራልና የሎጅስቲክ ስንቅ ሆኖት ወደ ኋላ ማፈግፈግ ሳይሆን ወደ ፊት ብቻ እንዲገፋ አስችሎታል ፡፡
በእነዚህ ዘመቻዎች ምኒልክ በአዳም ልጆች መለኪያ የማይለካ መለከታዊ ባህሪ ያለው ያህል ገዝፎ እንዲታይ ያደረገው ምኒልክ የደጃፉን ጎተራ አራግፎም ሆነ የበረቱን ከብት ጎትቶ አውጥቶ ሽጦ በገዛው ስናድር ፣ለቨን ( ነፍጥ ) ሳይሆን ምኒልክ የተጠቀመበትን መሳሪያ የተገዛው ቀደም ባለው በጉራጌና በኦሮሞ ዘመቻ በተፈነገለ ባሪያ በተገኘ ገንዘብ በተገዛ ነፍጥ ወይም በባሪያ ልዋጭ በተገኘ መሰሪያ በተፈናጠረ አረር ነው ፡፡ ለዚህም ነው የምኒልክ ወረራን በአጭር ቃል ‹‹ ሥጋን በኩበት ጠበሰት›› ስል ልቤ በደቂቃ 72 ምት ከመምታት ያላቆመው ፡፡
ሥጋን በኩበት በመጥበሱ ዘመቻ በ1875 ዓ/ም የጉራጌው አገር ለሸዋው ገዥ እጅ ሰጦ ገባ ፡፡ ይህ ታታሪ ሀዝብ ለሸወው ምኒልክ መግባን ተከትሎ የምኒልክ አቅም ይበልጥ ጎልብቶ የጊዜን ወንዝ ለመሻገር በአይኑ አማተረ በአግሩ መተረ ፡፡
በ1881 ዓ/ም ከታወቁ የምኒልክ የጦር አበጋዞች ዉስጥ አንዱ የሆነው ራስ ጎበና ዳጬ የተባለው ከሸዋ ተነስቶ ጊቤን ለመሻገር ያስቻለው አብይ ምክንያት የምኒሊክ በግራና በቀኝ መስፋፋት ያልጣመው ደጃች ካሳይ ( ካሳ ) ምርጫ የምኒልክን አቅም ለማዳከምና እርስ በእርስ ለማጋጨት በማሰብ ከምኒልክ ጋር መሳ ለመሳ ያልሆነውን የጎጃሙን ተክለሐይማትን የከፋን ግዛት ጨምሬልሃለው በማለት የከፋ ንጉስ አሰኝቶት ስለነበር የጎጃሙ ተክለ ሐይማት በራስ ደርሶ ( ደረሰ ሽፈራው ) የሚመራ ጦር በመያዝ ወለጋን (ነቀምትን ) ፣ጎማን ፣አሞሮ ፣ሐሮን፣ጉዱሩን፣ግምደበረትን እንዲሁም ጅማን አስገብሮ አስከ ከፋና ኮንታ እንዲሁም ኩሻ ( ሼ/ጊሚራ) እና ጫራ አስከ ጎልዲያ መድረሱንና የጎማውን ባላባት አባ ጆቢርን መግደሉን መረጃው ምኒሊክ ዘንድ የደረሰ ጊዜ ነው፡፡ የሸዋው የጦር መሪ በምኒልክ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በ181 ዓ/ም ከፋ ተብሎ ወደ ሚታወቀው ግዛት ጦራቸውን ንቀሳቀሱ ፡፡ የጎበና ዳጬ ጦር ብዙ ግዛቶችን ለሸዋው ምኒልክ እያገባ ሊሙ ሲደርሰ የጎጃሙ ራስ ደርሶ( ደረሰ ሽፈራው ) ከአገራቱ ያሰባሰበውን ብዙ የዝባድና የዝሆን ጥርስ ሊሙ ላይ አስቀምጦት አሱ ሰራዊቱን ይዞ ኩሻ እና ጎባ ጫራ ደርሶ ነበር ራስ ደርሶ ፡፡ ጎበና እንደደረሰ ራስ ደርሶ የተሰበሰበውን ግዳይ ‹‹ ዉሃ ለቀደመ ግዳይ ለተለመ ›› ሳይል ራስ ጎበና ሰብስቦ በእጅ አደረገ ፡፡
ዘፋኝም ፡- እነዚህ ጎጃሞች በምን ይስቃሉ ፣
ጥርሳቸውን (የዝሆን ጥርስ) ሊሙ ጥለውት ሔዱ
ሲሉ አዘመሩባቸው ፡፡ የጎጃሙ ራስ ደርሶ( ደረሰ ሽፈራው ) ግዳዩ በራስ ጎበና መበዝበዙን ሲሰማ ተግደረደረ ወደ ፊት ሔዶ ምርኮ ቢበዘብዝ አሁንም ለሸዋው ገዥ እንደሚያስረክብ የተረዳው ኩሻ ላይ ይህንን ያህል ሞልቶ ወደ ጎልዲያ መሻገርን የሚከለክል ወንዝ በሌለበት ጎጃሜዎች ለማታለል ዉሃ ሞልቶ ተመለስኩ በማለት ወደ ራስ ጎበና ሊሙ ተመለሰ ፡፡
አዝማሪ ግን ፡-
የኩሎው ፣የኮንታው፣ የገሚራው ፣የኩሻው ራስ ደርሶ
ውሃ ሞላ ብሎ መጣ ተመልሶ ፣
ሰው ካረጀ ወዲያ ልጅ አይሆንም መልሶ ፡፡
አሸሞሩበት ፡፡ የጎጃሙ ራስ ደርሶ( ደረሰ ሽፈራው ) ራስ ጎበና ጋ እንደ ደረሰ በሰይፍ ስለት ከሚገስጸው ይልቅ ‹‹ በዮሐንስ አምላክ ተዳኝ ›› አገሬን ለቀህ ዉጣ አለ ፡፡ የጎጃሙ ተክለ ሐይማት የሸዋዉን ምኒልክን ሁለቱም ራስ ደርሶና ራስ ጎበና ሊሙ ላይ ሊጣሉ ነበር ግን የሸዋው ጎበና ራስ ደርሶ ከሊሙ ፣ ከከፋ፣ጊሚራ፣ ኩሎ፣ ኮንታ ፣ጫራ፣ ከኩሻና ከጎልዲያ የበዘበዘውን ምርኮ ሸክፎ ወደ አዲስ አበባ እብስ አለ ፡፡
ለዚህም በስንኝ ሲቋጥሩ ፡-
እገዛለው ብሎ ከእንጦጦ ገስግሶ ፣
በዮሓንስ አምላክ አስኘው ደርሶ ›፡፡ ተባለለት
ምኒልክ በጎጃሙ ተክለ ሀይማኖት የተበዘበዘውንና በጎበና የተነጠቀውን ምርኮ ሲመለከት በእርግጥም ይህ ግዛት የናጠጠ ሃብታም መሆኑን በመገንዘቡ ቀጥታ የስሞታ ደብዳቤ ለዮሐንስ 4ኛ ላከለት ፡፡ ሁሉም ለጥቅሙ ነው ።ተክለ ሐይማትም በተመሳሳይ ዮሐንስ 4ኛ ከሸለሙት ከፋ ግዛት ዉስጥ ከሚገኘው የጫራ ሹሮ ሕዝብ ቆጥና ጎተራ ላይ ሳይቀር ጃኖ ዘርግቶ እየወቃ የበዘበዘውን ማሽላ ሳይቀር ራስ ጎበና ቀምቶት መውሰዱንና የተሸለመውን ግዛት እንዳይገዛ ሳንካ መፈጠሩን የተሰማዉን ቅሬታ ለዮሐንስ 4ኛ በደብዳቤ አቤቱታ አቅርቦለት ነበር ፡፡
አፄ ዮሐንስ 4ኛ ለደብዳቤያቸው መልስ ሰጠዋል ፡፡ ሆኖም ለጎጃሙ ተክለ ሐይማት የተላከው ፖስተኛ ደብዳቤውን ይዞ ወደ ጎጃም ሲመለስ አጋም ዉሃ ሲደርስ ደስታ ኃይሉ የተባለ ሽፍታ ፖስተኛዉን አንገላቶት ፖስታዉን ተቀብሎ ቀድዶ መጣሉ የተነሳ ተክለ ሐይማኖት የዮሐንስ 4ኛ መልስ ሲጠብቅ ሲጠብቅ በማጣቱ ጦር ለማንሳት የስንቅ ዝግጅት አደረገ ፡፡ ሴቶችም እንዲ ሲሉ በበሶ ማዘጋጀት ጀመሩ ፡-
ሴቶች ተሰብስበን እንውቀጥ ዳሂራ ፣
ክርክር አይቀርም ከራስ አዳል ጋራ ፣
ይታመሳል አሉ ከፋና ቦረና ፣
አማን አይደለም ወይ ራስ ጎበና ፡፡
ስንቁ ተሰናድቶ በተክለ ሐይማኖት በኩል የጦር ክተት አዋጅ የሆነው "" ጎስም ነጋሪት ክትት ሰራዊት ›› አዋጅ እንደታወጀ ምኒልክም መጋቢት 13 ቀን 1882 ዓ/ም ከእንጦጦ ተነስተው ግንቦት 30 ቀን አንቦቦ ሜዳ ላይ ከጎጃሙ ጦር ጋር ተፋጠጡ፡፡ በጦርነቱ አውዱማ ላይ የተክለ ሐይማት የገብስ ነዶ ለምኒልክ ገብስ ነዶ ወድቃ ሰገደች ፡ ተክለ ሐይማኖት በርካታ ቦታዎች ላይ ቆስለው ተማረኩ ( ሊሙ ጎጃሜዎች ላባቸውን ያንጠፈጠፉበት ፣አጥንታቸውን የከሰከስበት እንዲሀከም ደማቸውን ያፈሰሱበት አገር ነው ) ሆኖም ድል በምኒልክ የበላይነት ተጠናቀቀ ( በለስ ቀናው ) ፡፡ ምኒልክ ተክለ ሐይማኖትን ማርኮት ወደ እንጦጦ ወስዶ አክሞ ካዳነው በኋላ ራስ ደርሶ ፣ ደጃች ስዩም እና ሌሎችም የጎጃም መኳንንት ባሉበት ታላቅ ግብር ተደርጎ ተበልቶ ጠጅ እየተጠጣ ሲጫወቱ ምኒልክ የአንቦቦውን ጦርነት አንስተው ጎጃሞች በርትተው መዋጋታቸውን አድንቀው ተ/ሐይማኖትን እንደው እኔን ብትማርኩኝ ኑሮ ምን ታደርኝ ነበር ሲል ጠየቃቸው ፡፡ መኳንቶቹ ምላሹን ተ/ሐይማት እንዲመልሱ አይን አይናቸውን እየተመለከቱ ሳለ ጎጃሞች በንጉሳቸው ተ/ሐይማኖት በኩል ‹‹ ቆራርጠን ለአሞራ ነበር የምናበላዎት ›› ሲሉ መለሱ ምንልክ ከእናንተ ጭካኔና ከእኔ ርህራሔ የቱ ይሻላል ሲሏቸው ጎጃሞቹ በአንድነት ‹‹ ሲዋጉ ጨካኝ ድል ሲያደርጉ ርህሩሁ መሆን የሚገባ ነው ›› ብለው በአንድነት መለሱ ። ከጎጃሞች ይህንን ወደድኩላቸው ።ግብሩንም ጎጃሞች በጨዋታ አደሩት ፡፡እኔም ማርኮ ለሰማይ ሲላ ከሚሰጥ ጎጄዎች ይልቅ ማርኮ አክሞና ለሚጠገነው ለሸዌው ንጉስ እንኳንም ፈጣሪ አሳልፎ ሰጠን አልኩኝ ፡፡በዚህን ጊዜ ጀምሮ ከወደ ደቡብ ምዕራብም ሆነ ከምዕራብ ብቅ ብሎ የሸዋዉን ንጉስ አቅም የሚፈትሽ ጎበዝ በመጥፋቱ የተነሳ ይህ አከባቢ በሳህለ ሥላሴ የልጅ ልጅ በሆነው ምኒልክ ስር የምትጠበቅ አገር ሆነች ፡፡
ምኒልክ ወደ አቦቦ ጦርነት ከመምጣታቸው በፊት በታላቁ ሀረር የጀመሩትን ጦርነት ከዚህ ጊዜ በኋላ በ1887 ዓ/ም አሚር አብዱላሒን ድል በማድረግ አጠናቀው የሸዋ ወታደሮች ( የምኒልክ ወታደሮች ወይም የምኒልክ አማሮች ) ከወለጋ በስተደቡብ ምዕራብ ተንቀሰቅሰው ኢሉባቡርን ያዙ ፡፡ አሉባቡር በሸዋው ገዥ ስር ሲገባ ደጃች ተሰማ ናደው የኢሉባቡር ገዥ ተብለው ተሰየሙ ፡፡ ደጃች ተሰማ ናደው ግዛቱን እያደላደሉ ሳሉ በ1888 ዓ/ም አገሪቱን የጣሊያን ወራሪ ኃይልን የመመከት አደጋ ስላጋጠመው የምኒልክ የመስፋፋት ጉዞ ለሁለት ዓመታት ያህል ጊዜ የተገታ ሲሆን ለአድዋ ጦርነት ደጃች ተሰማ ናደው( የአሉባቡሩ ) እና ራስ ወልደ ጊዮርጊስ አቦዬ ( የከፋው ) ከአገራቸው ርቀት የተነሳ በአድዋ ጦርነት ላይ ሳይሳተፉ ቀርተው ወደ ሐረር በመዝመት ከጣሊያን ጋር ለማበር የቃጣዉን መሐመድ አንፋሪምን ተዋግተው ድል አድርገውታል ፡፡በቀይ ባህር ጠረፍ እና በኢትዮጵያ ግዛት አቋርጦ የኢትዮጵያን አንድነት ለመፈታተን የመጣዉን የጣሊያንን የታጠቀ ዘመናዊ ሰራዊት ከኢሉባቡርና፣ከከፋና ከጎልዲያ -ሩዶልፍ ሐይቅ ካለው ግዛት ለጦርነቱ ተወጣጥቶ መዝመት ካለበት ዉጭ ከመላው ከኢትዮጵያ አንዳንድ ክፍል ብቻ በዘመተ አርበኛ ብርቱ ተጋድሎ የጊዜው አቢሲኒያ ወይም ኢትዮጵያ በድል ታጅባ ጦርነቱን ስታጠናቅቅ በዓለም ሁሉ ተደራሽ የሆኑ ጋዜጦች ላይ በመጀመሪያው ገጻቸው ላይ የአፄ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ቡጡል ፎቶ ግራፎችን በማውጣት የጣሊያን ምንግስት ከደረሰበት ቁሳዊና ሰበዓዊ ኪሳራ በተጨማሪ የሞራል መንኮታኮትን ጨምሮበታል፡፡በዚህ ምክንያት የአደዋ ጦርነት ላይ ጣሊያንን ድል የተቀዳጀችው ባለቤት ማንነትን ከዘመናዊ የዓለም ካርታ ላይ ለመፈለግ የማናበቢያ መነጽሩን ያላስተካከለ ፊደል የቆጠረ የዓለም ፍጡር አላነበረም ፡፡ሆኖም ጦርነቱ ኢትዮጵያን በዘመናዊ የዓለም ካርታ ላይ ስሟን ያካተተ እና ኢትዮጵያ ከተዘጋችበት ዋሻ አውጥቶ ሥሟ ፀሐይ ባየው አገር ሁሉ በአደባባይ ያወጣ ታላቅ ድል ሆነላት ፡፡ስለሆነም በአባይና በኦሞ ተፋሰሶች መካከል በሚገኘው ሰፊ እና ለም መሬት ላይ አዲስ የመስፋፋት ዕቅድ ተይዞ ከጣሊያን በተማረከው መድፍም የታጀበ ዘመቻ ተጀመረ ፡፡
ዘመቻዎቹ 1ኛ/ የራስ ወለደጊዮርጊስ ጦር የከፋ ግዛትን አካል ከሆኑት ጎፋና ኮይሻን ከተቆጠጠረ በኋላ የሸርማ ወንዝን በማቋረጥ ከጎልዲያ አስከ ስጢፋኒ ( ሩዳልፍ ) ሐይቅ ዳርቻ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ያሉትን አገሮች በሙሉ እንዲይዝ ተልዕኮ አንግቦ ከሌላ ገለዜ በተሻለ ሁኔታ የታጠቀ 30000 (ሰላሳ ሺ ) ወታደሮች ተመደቡለት ፡፡
2ኛ/ ደሌላው አዝማች ደጃች ተሰማ ናደው ሲሆኑ ከከፋ በስተሰሜን ያሉ ሕዝቦችን ለማስገበር በተመሳሳይ 8000 ( ስምንት ሺ )ወታደር ይዞ የባሮን ወንዝ ተሸግሮ ወደ ነጭ አባይ አቅጣጫ እያመራ አዳዲስ ግዛቶችን እያስገበረ ከአታላንቲክ ውቂያኖስ ተነስቶ ወደ አባይ የላይኛው ክፍል በመገስገስ ላይ ከነበረው ከሻንበል ማርሻድ ከሚመራው የፈረንሳይ ክፍለ ጦር ከሴኔጋል ክፍለ ጦር ጋር ተገናኝቶ የነጭ አባይ (የሶባት ወንዝ ) ታችኛው ክፍልና የአባይ ላይኛው ክፍል እንደቆጣጠር ተልዕኮ ተሰጦት ነበር ፡፡
3ኛ/ በራስ መኮንን የተመራ ዘመቻ ሲሆን እሱም ቤኒሻንጉልን ለማስገበር የታለመ እንደሆነ ከማወቅ በቀር በዚህኛው ረገድ ጠለቅ ያለ ጥናት ባለማድረጌ በደጃች ተሰማ እና በራስ ወልደ ጊዮርስ የተመራዉን ዘመቻ ግን ሰተራ በተራ ለማስቃኘት እሞክራለው ፡፡
በደቡብም ምዕራብ ኢትዮጵያ የሠላዉን የመኒልክ ጎራዴ በመያዝ ሕዝቦችን ቀጥቅጦ ወደ ማዕከላዊው የሸዋ ግዛት በማዋሐድ የታወቀው ራስ ጎበና ዳጬ ነው እንጂ ምኒልክ እንደ አሩሲና ወላይታ ራሳቸው ሰይፍ መዘው አልተዋጉም ፡፡ ጎበና ጎበና ሉሙ ( እናርያ )፣ጎማን፣ ጌራን፣ጂማን እና ከፋን ካዳከመ በኋላ ነው ለደጃች ተሰማ እና ራስ ወ/ጊዮርጊስ ያስረከቡት ፡፡ ጂማ በምኒልክ አማሮች ከተወረረች በኋላ የጂማው ዳግማዊ አባ ጅፋር ወደ አንኮበር ተወስደው የታሰሩት በራስ ጎበና ደጬ ዘመቻ ታግዘው ነው ፡፡
ተብሎለትም ነበር ፣--- እመ ሠላስ ቀን ፣ጎበና ባይፀና ፣
ይካፈሉን ነበር ፣እነ ቱፋ ሙና ።( ቱፋ ሙና በወቅቱ ይፈራ የነበረ የአብቹ ባላባት)
እዚህም "ስጋን በኩበት ጠበሱት "ለማለት ያስደፍራል ፡፡ የአባጅፋር አንኮበር ተወስዶ መታሰር "ገባው " ያለውን ጋኪ ሻርቾን "ወጣው " አሰኝቶት ‹‹ ዱር ቤቴ ››እንዲል ገፋፋው ፡፡ የጎጃምን ተክለ ሐይማኖትን ታግሎ የጣለው ምኒልክ ዳግማዊ አባ ጅፋር በኦሮሞው ጎበና በኩል ለአንድ አመት አንኮበር ላይ በእስር እንዲቆይ ካደረገው በኋላ ዙፋኑን መልሶለት ታማኝ እንዲሆን አድርጎ ለጂማ ገዥ አድርጎ ሸልሞት ሾመው ፡፡ አባ ጅፋርም ፍፁም ታማኝ ከሆኑት የሸዋ አጋሮች( የምኒልክ አማሮች ) ዉስጥ እንደ አንዱ ተቆጥሮ ከምኒልክ ጋር ግንኑነቱን ያዘለቀ ሲሆን በኋላም የከፋው ዘመቻ ላይ በተጨባጭ ታማኝነቱን አሳይቷል ፡፡
በኋላም ደቡብ ምዕራብ ያሉ አከባቢዎች የተካሔዱ ዘመቻዎች በሙሉ ከጅማው አባጅፋር አጋዥነትና ታማኝነት የተካሔዱና ሸዋዎችም ድልም የተቀዳጁበት መሆኑን ለቦታዎች በተሰጡ ስያሜዎች እና እኔ የምኒልክ አሽከር ወይም ያባጤና ( የኢያሱ ለማለት ) ብለው የሚፎክር ባቹማ ላይ አጋ አባሙራ ጎሪ ጌሻ ላይ ማሞ ቀነኔ እና ማሞ እጅጉ ከወደ ማጀ / ቱም/ ደግሞ ገርባ ፣ወልቀባ ወዘተ ብዙ ነበሩ ፡፡ጉራ ፈርዳ ብለው ቡክቱ ያለውን ተራራ የሰየሙት ኦሮሞዎቹ የምንልክ አማሮች ናቸው ። ማዕከሉን ጅማ ያደረገና በጅማው የኦሮሞ ፈረሰኞች ታግዞ በደጃች ተሰማ ናደውና በራስ ወ/ጊርጊስ አቦዬ የተመሩት ስምንት ሺ ና ሰላሳ ሺ ወታደሮቹ በተከታታይ ከኦሮሞና ከጉራጌ ባሪያዎች ተግዞ የተገዛው ለበን አረር እንዲሁም ከጣሊያን በተማረከ መድፍ መኤን ( ሹሮ) (ቲሻና ) ተቀጥቅጠውና እነሱም ቀጥቅጠው ነው ማዕከላዊው መንግስት እጅ የሠጡና በቀያቸው የኢትዮጵያው አርጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዲራ እንዲከበር ያደረጉት ፡፡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የምኒልክ አማሮችን በጀግንነት ከተዋጉ ሕዝቦች ዉስጥ ሹሮ( ቲሻና) ከከፋ ህዝቦች ቀጥሎ ሁለተኛ ናቸው ፡፡ ወደፊት በስፋት መጣበታለው ፡፡ እነ ደጃችና ራስ እግረ መንገዳቸውን አዳዲስ ግዛቶችን ማጠቃለል በመሆኑ በዚህ የተልዕኮ ዘመቻቸው የኢሉባቡርን ግዛት የኢትዮጵያ አካል መሆኗንና የማሰንጌንና የጊሚራን እንዲሁም የጉረፈርዳን ግዛት ማስገበሩን ለንጉሰ ነገስቱ መስከረም 15 ቀን 1898 ዓ/ም በሪፖርት አቀረቡ ፡፡ በዚህን ጊዜ የኢሉባቡር ኦሮሞዎች ጉራ ፈርዳ ( የፈረስ ጆሮ ) ሲሉ የሰየሙት ተራራ ያለበት ግዛት ዉስጥና ዙሪያዉን በዋነኘነት የሚኖሩት የሹሮ ( መኤን፣ ቲሻና ) ሕዝብና የሸኮ ሕዝቦች በመሆናቸው ደጃች ተሰማ ናደው ለጊሚራ አውራጃ ገዥ እንዲሆኑ ደጃች ሙሉጌታ ይገዙን ፣ ለጉራ ፈርዳ አውራጃ ገዢ እንዲሆኑ የጉራፈርዳ አውራጃ አንዱ ክፍል ከሹሮ ብሔረሰብ የኮሉ ጎሳ መሪ ባላባት የነበሩትን ሲያፍጫጫ መስሚያ የሌለውን ባላባት ሲቂዮ ጃውቶን በመሸለምና በመሾም ቀኝ አዝማች አስኝቶ ቀኛዝማች ሲቂዮ ጃውቶን በኋላም ክርስትና ተነስቶ ካበቃ በኋላ ገብረ መድሕን የሚል የአማራ ስም ተችሮት ሹመቱ ከፍ ብሎ ፊታውራሪ ሲቂዮ ጃውቶን ለአከባቢው ገዥ ሲያደርጉት ከሸኮ ብሔረሰብ ከዲጊያብ ጎሳ ባላባት የሆነው ዴኩ ከሺን ግራዝማች አሰኝቶ ሹሞና ሸልሞ ደጃች ተሰማ ናደው ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓ/ም በምንልክ ለተነገረ የኑዛዜ አዋጅ ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው ተሰኝተው ለአቤቶ እያሱ ሞግዚትና እንደራሴ ተደርገው ወደ አዲስ አበባ አስከሚሔዱበት ጊዜ ድረስ የጉራፈርዳን አውራጃ በጋራ ሲያቀኑ ከነበሩት ዉስጥ ተጠቃሾቹ ቀኛዝማች ሲቂዮ ጃውቶን ( በኋላም በክርስትና ስሙ ገብረ መድሕን ) እና ግራዝማች ዴኩ ከሺን ናቸው ፡፡
ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው የአቤቶ ኢያሱ ሞግዚትና እንደራሴ ሆነው በበዓል ፣ በፍርድ ፣በችሎት አዳራሽ እና በግብርም ላይ በክብር ቦታ እያስቀመጡ ለሕዝብ እንዲታዩ እና ከሕዝብም ጋር እንዲለማመዱ እንዲሁም ለአስተዳደር እንዲበቁ ሲያደርጉ የእንደራሴው ግዛት ስለነበረው ደቡብ ምዕራብ ለልጅ ኢያሱ ምን ሹክ እንዳሉት ባጠና ባጠና ለማግኘት ባልችልም የልጅ ኢያሱ ሞግዚት ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው ከሞተ በኋላ የጊሚራ ዘመቻ ተብሎ የሚታወቀውን ዘመቻ ኢያሱ የመራበት መንገድ የበቀል እንጂ ለአንድ "ገባቻለው" ላለ ኢትዮዽያዊ ዜጋ የሚመለስ ምልሻ አልነበረም ፡፡ ነው ለጥ ብሎ ለገባው ምላሹ ይኼ ነው ።የጊሚራን ዘመቻ ታሪክ የአቤቶ ኢያሱ አጥንት ወደ ትቢያነት ተቀይሮ እስኪበን ድረስ እንደ እቶን አሳት ያቃትለዋል ፡፡ ለዘመቻው ምክንያት ነው የተባለው የጊሚራ አውራጃ ገዢ የሆነው ደጃች ሙሉጌታ ይገዙ ኢያሱ አባቱን ለማሾምና ንጉስ ለማሰኘት ከአባቱ ከራስ ሚካኤል ጋር ደሴ እያሉ ነው አኝዋክ ወይም ጃምቦ የተባለው ጎሳ ድንበር ተሸግሮ ወደ ሱዳን በመሔድ በሱዳን ዉስጥ የሚገኙትን ጎሳዎች ወግተው በመግደል ከብቶቻቸውን ዘርፈው ዘራፊዎቹ ወደ ሕግ መጠው እንዲቀጡ ብልክም አሻፈረኝ በማለታቸው የአኘዋክና የጃምቦ ሕዝቦች አምፀውብኛልና ልጅ ኢያሱ መጦ መላ እንዲሉ ደብዳቤው ደሴ እንደደረሳቸው ነው ፡፡ ልጅ ኢያሱ ይህንን ደብዳቤ እንደተቀበሉ "ታናሹ ጣትህ ከአባትህ ከምኒልክ ወገብ እንድትወፍር አድርግ " ብሎ ልክ በ2ኛ ዜና ምዕረፋ 20 ቁጥር 10 ላይ እንዳሉ የአንገተ ደንደሰኖቹ አይሁዶች መካሪዎች ሞግዚቱ ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው የመከረው ይመስል ልጅ ኢያሱ በጊሚራው ዘመቻ የፈጸመውን ወረሳ ( ወረራ) የሚያስኮንናቸው እንጂ የሚያስመሰግናቸው አይደለም ይላል መርስዓ ኃዘን ወልደ ቂርቆስ የዘመን ትዝታዬ ካየዉትና ከሰማዉት (1896 -1922 ) በተሰኘው መፃፋቸው ፡፡ በበዚህ ዓመተ ምህረት በ1904 ዓ/ም በጊሚራ ዘመቻ ጊሚራ ደርሰው አገሩን በሙሉ ወረሳ(ወረረ ፣ዘረፈ፣አገር አጠፋ) መቱት ወታደሩ ሁሉ የማረከውን ማርኮ የገደለውን ገድሎ ሁሉም መራዉን(ቁጭቱን ፣እልሁን) ተወጣ የብዙዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሕይወት ጠፍቶ ነበር ። የሰዎችን ጭፍጨፋ እንደ መልካም ሙያ ቆጥረው እንዲህ ሲሉ ዘፈኑላቸው ይላሉ መርሰዓ ኃዘን
አሞራው ዞረ አሞራው ዞረ ፣
አበላው ኢያሱ ሥጋ እየመተረ፡፡
የኢያሱ ጎራዴ በሐር የተሰፋው ፣
እያመመው መጣ ደም እየከረፋው ፡፡
በዘመቻው የተሳተፈው አቶ ወልደ ኪሮስ የተባለ የአቤቶ ኢያሱ ወታደር በወቅቱ ኢያሱ ነባር የምኒልክን ወታደር እናንተ የአባቴ ሙኩቶች ብሎ ከዘመቻ ስላስቀራቸው በኋላ ከልጅ እያሱ ጋር የዘመቱ ትኩስና ወጣት ወታደሮች በመሆናቸው የጊሚራ ዘመቻ ተብሎ በሚጠራው የደረሰው የሰባዊ ኪሳራ በምኒልክ ጊዜ እንኳ አልተፈጸመም ፡፡ አገሬ ኢትዮጵያ ይሁን ያለው አርብቶ እና ዘላኑ ሕዝብ በኢያሱ ጎራዴ ተቀላ ክርነ ረጃጅም ሴቶች ለጠጅ ጋን አጣቢነትና ለቨን ለመለወጫ ጉልበተ ጠንካራ ደረተ ሰፊ ወንድ ለእርሻ በሚል በዚህ ዘመቻ በርካታ የባሪያ ፍንገላ ተፈጽመዋል ፡፡
ተባለለትም ፣---- የማጂ ኩሪ ልጅ ዓይነ ትለፈፈቋ ፣
የደካራሻ ልጅ ግንባረ ስንጥቋ ፣
ቢለውጧት ለቨን ቢያቅፏት መሞቋ።ተዘፈነ
ከጊሚራ ዘመቻ በኢያሱ የተፈነገሉ ባሮች አዲስ አበባ ተግዘው በአቤቶ ኢያሱ ግቢ አቅራቢያ ወደ እንጦጦ ማሪያም ቤተክርስቲያን በሚወስደው መንገድ ዳር በቀኝና በግራ እንዲስሩ ስለተደረገ ጎጆ እየሰሩ ተቀመጡበት በዚህ የተነሳ የቦታው ስም ጊሚራ ሰፈር ተባለ ሲል የታሪክ ተመራማሪው
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1848 – 1966 ዓ/ም ሲሊ በሰየሙት የታሪክ መፀሐፋቸው ላይ ልጅ ኢይሱ በ1904 ዓ/ም ራሱ ጊሚራ ላይ ባካሔዱት ኢሰበዓዊ ዘመቻ 40000( አርባ ሺ ) የሚያህሉ ጊሚሮችን በባርነት አግዟቸው ወደ አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አከባቢ የጊሚራ ሰፈር በሚል ሰይሞ አስፍሯቸዋል ፡፡ሆኖም ከማጂና ከከፋም በተመሳሳይ አያሌ ተመሳሳይ ባሮችን አግዟል ሲል አባቱ ምኒልክ የባሪያንግድ አስቁሟል የሚለውን ኩሸት በአሳማኝ ማስረጃ አረጋግጦልናል ፡፡ የሌሎች ፀሐፍቶችን መረጃ እያገላበጥኩ ነው መረጃዎቹን ሳጠናክር ዘመቻው የጊሚራ ዘመቻ እንዲባል ያስቻለው አሳባቂው የልጅ ኢያሱን አልጋ መውረስ ሳይሆን የእቴጌ ጣይቱን የበላነት ሲያቀነቅን የነበረና በዲሞሺን ወደ ጊሚራ የተወረወረው በደጃች ሙሉጌታ ይገዙ በመሆኑ ችግሩን ከጊሚራ ነው ተብሎ አራገቡት እንጂ ችግሩ ተከሰተ የተባለው በሱዳን ድንበር አከባቢ ባለው በአኝዋክና በሱዳን መካከል ነው ፡፡ እንሁም ልጅ ኢያሱ የጊሚራ ከተባለው ዘመቻ በኋላ ወደ ጋምቤላ ነበር ለማቅናት ያሰቡት ጥታ ተሰግቶ ቀረ እንጂ ስለዚህ ያ ሁሉ ባሪያ የተጋዘው ከጊሚራ ብቻ አይደለም ፡፡ አገሩን በሙሉ ወሬሳ(ወረረ ፣ዘረፈ፣አገር አጠፋ) መቱት እደተባለ ሁሉ ከጉራ ፈርዳ ሹሮዎችም ፣ ከሸኮዎችም ከአኝዋኮችና ከጃምቦዎች ከሱዳን ቱፈሰሰዎች ዉስጥም የተቀላቀሉም በርካቶች አሉ ።በወቅቱ ከሁሉ ጎላ ያለው የራሱ የሹሮ ባላባት የሚል ማህተም ያለው ፊታውራሪ ሲቂዮ ጃውቶ ስለሆኑ ከተጋዙት ባሮች ዉስጥ እንጦጦ ማሪያም ቤተክርስቲን በሚወስደው መንገድ ዳር በቀኝና በግራ እንዲስሩ ተደርጎ ጎጆ እየሰሩ ከተቀመጡት እንዲሁም አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አከባቢ ጊሚራ በተባለው ሰፈር የሽሮ ቋንቋ ተናጋሪ ያለ በመሆኑ በሒደትም ከጊሚራ ሰፈር ይልቅ ሹሮ ሰፈር ወይም በኋላ ሹሮ ሜዳ እየተባለ እንደሔደ የሚጠቁሙ ብዙ ማስረጃዎች አሉ ፡፡ ምክንያቱም ያንን ሰፈር ሹሮ ለማለት የሚያስችል በዛን ጊዜ እዛ አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አከባቢ የሚሸጥ የሽሮ ገበያ ሊኖር ቀርቶ አተር ከቆሎና ከክክ ወጥነት ወጥቶ ሽሮ ሆኖ መበላት የጀመረው ከእኔ እድሜ በኋላ ነው በአፄዎቹ ጊዜ ሰው ጮማ በጠጅ ከማወራረድ በቀር ፡፡ ይቀጥላል ፡፡ ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ/ም ፡ሚዛን

Comments
Post a Comment